| Forum Home > Members Discussion > What happened to Political Parties' discussion forum (Amharic) | ||
|---|---|---|
|
Site Owner Posts: 139 |
Source: Reporter;
አራተኛው አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ተጠናቆ የድምፅ ቆጠራው ውጤቱ ይፋ ከሆነ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በቅድሚያ ጊዜያዊ ውጤቱን ቀጥሎም የማጠቃለያ ውጤቱን በየደረጃው ይፋ ሲያደርግ ግን ያለምንም ተቃውሞ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራቲክ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በምርጫው ወቅት ደረሱብን ያሉትን በደሎች ከምርጫ ቦርድ ጀምሮ በተዋረድ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ አሰምተዋል፡፡ የእነዚህ ሁለት ፓርቲዎች አቤቱታዎች በተለያየ መልኩ የቀረቡ ቢሆንም፣ እንዲሁ በጥቅሉ ጉዳዩን ለሚቃኝ ሰው ግን ተመሳሳይ ይዘት እንዳላቸው ለማየት አይቸገርም፡፡ በምርጫው በተሣተፍንባቸው አካባቢዎች ታዛቢዎቻችን ተባርረዋል፣ በምርጫው ዋዜማም ዕጩዎቻችን ተንገላተዋል የሚሉትን ቅሬታዎቻቸውን ይዘው አቤት ያሉት እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች፣ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተከናወነ የምርጫ ውጤት ውድቅ ሊሆን ይገባል፤ በምትኩ ደግሞ ድጋሚ ምርጫ መካሄድ አለበት ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ከቦርዱ ጀምሮ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ምላሹ አንድና አንድ ነበር፡፡ ይህም አቤቱታችሁ ተገቢውን መሥመር የተከተለ አይደለም፣ ያቀረባችሁት ማስረጃ አጥጋቢ አይደለም፡፡ ስለዚህም ክሱ ሕጋዊነት የለውም የሚል ነው፡፡ የሕግ አካላቱ ሐሳብና የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ግን ለፓርቲዎቹ የሚዋጥ አልነበረም፡፡ ነገር ግን 499 የተወካዮች የምክር ቤት መቀመጫ ያሸነፈውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግን) በአገሪቱ የአንድ ፓርቲ መንግሥት የማቋቋም ህልሙን ተግባራዊ እያደረገ ነው ከማለት ያለፈ መራመድ አልቻሉም፡፡ የሆነ ሆኖ አሁን የቃላት ጦርነት እያስተናገደ ያለው ምርጫ 2002 በዋዜማ ግድም፣ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ፓርቲዎቹ አብሮ በጋራ የመሥራት አዝማሚያ ያሳዩበት እንደነበር መታወስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ጥር 2002 ዓ.ም. ገደማ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ"፣ ቅንጅት፣ መኢአድና ኢሕአዴግ የጋራ የምክክር መድረክ ማቋቋማቸው ከላይ ከተጠቀሰው ሐሳብ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆን ነው፡፡ ኋላ ላይ በርካታ ፓርቲዎች የተቀላቀሉት የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በእርግጥ የጋራ ችግሮች ላይ ለመወያየት ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ለዚህ ምስክርነት በፖለቲካው ትዕይንት እምብዛም የታወቁ ካልሆኑ ፓርቲዎችም ሳይቀር ይሰጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፓርቲያቸውን ድል ተከትሎ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ በቀጣይ በምርጫው ውጤት ያልተሳካላቸውን ፓርቲዎች ለማሣተፍ ዕቅድ እንዳለ መግለጻቸው ሲታይ፣ የዚህ የጋራ ምክር ቤት ዕጣ ፈንታ በዚሁ ዕቅድ ውስጥ ይጠቃለል ይሆን? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የመስቀል አደባባይ ንግግራቸው ፓርቲያቸው የሚመሠርተው መንግሥት በተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላገኙትን ፓርቲዎች በምክክር ደረጃ ያሣትፋል፣ በልማትና በአጠቃላዩ አገራዊ የሆኑ አጀንዳዎች ከነዚሁ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የሚመከርበት ይሆናል ሲል ቃል ገብተዋል፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ የወደፊት ዕቅዱ በዚህ መስመር የሚሄድ ይሆናል ሲል፣ በሌላ በኩል የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ለዕቅዱም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ምላሽ የሚሰጡበት ወቅት ላይ አልነበሩም፡፡ ከሞላ ጎደል በአሁኑ ወቅት ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ፓርቲዎች የፍርድ ቤት ውሳኔ ደርሷቸዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችን በተመለከተም ቢሆን አቤቱታ የማቅረቢያ ጊዜው የተገባደደ በመሆኑ ስለ የጋራ ፓርቲዎች ምክር ቤት የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚታሰብበት ጊዜ ስለመሆኑ የፖለቲካው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ የጋራ ምክር ቤት አማካይነት ከምርጫው በፊት ማለትም ከጥር እስከ ግንቦት 2002 በነበረው ጊዜ ውስጥ ፓርቲዎቹ እንደየአስፈላጊነቱ በየሳምንቱ ረቡዕ እየተገናኙ ሲመክሩ ከርመዋል፡፡ አሁንስ የምርጫው ሒደት ከተጠናቀቀ ሁለት ወር ግድም ሆኖታል፤ ታዲያ የዚህ መድረክ እንቅስቃሴ የት ላይ ይገናኛል? ወደፊትስ መንግሥት እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በቀጣይነት መድረኩን እንዴት ለመጠቀም አስበዋል? ከምርጫው ወዲህ ምክር ቤቱ ምን እየሠራ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅም ወቅታዊ እና ተገቢ ይሆናል፡፡ ከመጨረሻ ጥያቄ ብንነሳ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ፓርቲዎች እና የምክር ቤቱ አስተባባሪ አካላት እስካሁን ድረስ ማለትም ከምርጫው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ በጋራ ምክር ቤቱ አልተገናኙም፣ እንቅስቃሴም የለውም ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) ሊቀመንበር አቶ ግርማይ ሀደራ፣ የምክር ቤቱ ከምርጫው በኋላ ጠንክሮ ያለመሥራት በፓርቲዎቹ መካከል ብልጭ ብሎ የነበረውን የመወያየት ባህል እያጠፋው ነው ይላሉ፡፡ ሊቀመንበሩ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ፓርቲያቸው እንደ መድረክ እና መኢአድ ወደ ፍርድ ቤት የመኼድ ዓላማ ባይኖረውም፣ በተወዳደሩባቸው አምስት ክልሎች ውስጥ ደርሶብናል ያሉትን በደል ለማንሳት እና ከሱ ትምህርት ለመውሰድ መድረኩ ዓይነተኛ መሣርያ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ to be continued . . . . | |
| ||
|
Site Owner Posts: 139 |
. . . . . Continued
በሌላ በኩል አቶ ሙላት ጣሰው የብርሃን ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ (ብአዴፓ) ፕሬዚዳንትም ተመሳሳይ ሐሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለምርጫ ቦርዱ በመረጃ አስደግፈው የምርጫ ግድፈቶችን በተመለከተ አቤት ቢሉ ተገቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን፣ ስለዚህም የጋራ ምክር ቤቱ ጥቅም እዚህ ላይ ነበር ይላሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ከላይ የተመለከቱት ሁለቱም የፓርቲ አመራሮች የጋራ ምክክር መድረኩን ከተኛበት መቀስቀስ ካልተቻለ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ እንደሚመጣ ያስረዳሉ፡፡ የብአዴፓ እና የኢፍዴኃግን የምርጫ አቤቱታ በተመለከተ የቦርዱ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ መንገሻ በሰጡት ምላሽ፣ የፓርቲዎቹ ጥያቄ በወቅቱ ተስተናግዶ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ የሆነ ሆኖ ፓርቲዎቹ ያሰመሩበት ጉዳይ ግን በተደጋጋሚ በተለይ በምርጫው ማግስት ምክር ቤቱ እንዲገናኝ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ የመሆኑን ጉዳይ ነው፡፡ "ከምርጫው በኋላ በነበሩ ተከታታይ የመሰብሰቢያ ቀኖች ወደ ምክር ቤቱ ደውለን ነበር፤ ነገር ግን እንቅስቃሴ አልነበረም" ይላሉ አቶ ግርማይ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጹ፡፡ ዕውን ምክር ቤቱ እንቅስቃሴውን እስከወዲያኛው አቁሟል? አቶ እሸት ገብሬ የጋራ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ለዚህ ምላሽ አላቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ምክር ቤቱን የመሰብሰብ ሥልጣን ለአንዱ ወይም ለሁለቱ ፓርቲዎች አለበለዚያም ለጽሕፈት ቤቱ የተሰጠ አይደለም፡፡ ፓርቲዎቹ በተለያዩ መንገዶች ይገናኙና የጋራ መድረኩ እንዲጠራ ለጽሕፈት ቤቱ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ በዚህ መሠረት ምክር ቤቱ ይሰበሰባል፡፡ አቶ ሞሼ ሰሙ የኤዴፓ ጸሐፊ ግን ከዚህ ጋር የሚስማሙ አይመስሉም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከምርጫው በፊት በነበረው ሒደት ምክር ቤቱ ሁሌም ስብሰባውን ጨርሶ ሲለያይ ቀጣዩ አጀንዳ ምን መሆን እንዳለበት ይወስን ነበር፡፡ በዚያውም የመገናኛ ቀኑንም ያስቀምጥ ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን በመጨረሻው ስብሰባ ዕለት የነበረው ሁኔታ የምክር ቤቱን የወራት እንቅስቃሴ መገምገም እና ወዲያውም ፓርቲዎቹ ወደየግል የምርጫ እንቅስቃሴያቸው መለያየት ነበር፡፡ ስለሆነም በወቅቱ ምክር ቤቱ በመቀጠል የሚገናኝበትን ረገድ ለመወሰን የተደረገ ነገር አልነበረም፡፡ አቶ ሞሼ አክለው እንደገለጹት፣ የምክር ቤቱ ሥልጣን እና ኃላፊነት በጋራ ስምምነት ላይ በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየት እንጂ፣ ከላይ እንደተነሳው ከምርጫ ጋር በተያያዘ ስለተከሰቱ ችግር መነጋገርም ሆነ መፍትሔ መስጠት አይደለም፡፡ ይህንን ለማድረግ አቅምም የለውም፡፡ እንደ ብአዴፓ እና ኢፍዴኃግ ላሉ ፓርቲዎች ግን ምክር ቤቱ ከዚህ ላቅ ያለ ሚና እንዲጫወት ይጠበቅበታል፡፡ የዚህ ምክር ቤት የወደፊት እጣ ፈንታን በተመለከተም አቶ እሸት እንደሚሉት፣ መንግሥት በይፋ ከፓርቲዎች ጋር መድረክ ፈጥሮ ለመሥራት የገባውን ቃል ዕውን የሚያደርግበት መድረክ እንደሚሆን ነው፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ እሸት፣ በአሁኑ ወቅት ከምርጫ በፊት እንደነበረው ዓይነት በየሳምንቱ የሚገናኙበት አካሔድ የለም፤ ፓርቲዎቹ ዝግጁ ከሆኑ ግን የመቀጠል አቅሙ አሁንም አለ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የምክክር መድረኩን አስፈላጊነት የሚጠራጠሩም እንዲሁ አልጠፉም፡፡ አቶ ያዕቆብ ልኬ የመኢአድ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ በጉዳዩ ላይ ሲናገሩ፣ "ኢሕአዴግ በምክር ቤቱ ያጸደቅናቸውን ሕጎች የጣሰ በመሆኑ፣ ምክር ቤቱን መልሶ መሰብሰብ ትርጉሙ አይታየኝም፤" ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው በዚህ በኩል የሚመጡ ግብዣዎችንም ለመቀበል ዝግጁነትም የለውም ብለዋል፡፡ ከሞላ ጎደል ግን ፓርቲዎቹ የምክር ቤቱን አስፈላጊነት በየራሳቸው መንገድ ሲገልጹት ይታያል፡፡ ይህ መድረክ መንግሥት ቃል በገባው መሠረት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱ ይሆን? | |
|
--
| ||