የኢትዮዽያውያን ዴሞክራቶች ድረ-ገፅEthiopian Democrats' Website

New Generation for Democracy in Ethiopia

Forums

Post Reply
Forum Home > Members Discussion > Tewodros II & Tewodros III

Tewodros Salsawi
Member
Posts: 24

በ17ኛወ ክ/ዘመን በዘመነ መሳፍንት ነው። በጊዜው ስሁል ሚካኤል በግል ብልጠት እና ጥረት ይዘውት የነበረውን ስልጣን ራስ አሊ ትልቁ በህዝብ ግፊትና በ አዋጅ ጨበጡት። በዚህ አኳሁዋን ለ76 አመታት የገነነውን “ዘመነ መሳፍንት” ተብሎ የሚጠራውን የ ኢትዮዽያ ታሪክ ምእራፍ ከፈቱ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በ1966ዓ.ም በተነሳው የህዝብ አመፅ ንጉሰነገስት ሃይለ ስላሴ በግል ብልጠትና ጥረት አደላድለውት የነበረውን ስልጣን በህዝቡ ግፊት ሆኖም ህዝቡ ባልፈለገው ሁኔታ ደርግ ሲረከብ ዘመነ ጥላቻ ተጀመረ።

.............

በዘመነ መሳፍንት ለ76 አመታት መሳፍንቱ እኔስ እንደራስ ዓሊ ስልጣን መያዝ አልችልም እንዴ? ማን ከማን ያንሳል? እያሉ እድላቸውንና ጉልበታቸውን ለመሞከር ቆርጠው ተነሱ። የሁከት የብጥብጥ የብዙ ውጊያ አመታት ሆኑ። ስልጣኑን እነ ራስ ጉግሳ፣ እነራስ ወለደየስ፣ እነራሰ እገሌ እነራስ እነቶኔ ተነጣጠቁት።

በተመሳሳይ መልኩ በዝቅተኛ መኮንኖች አባልነት ለጊዜያዊ ጉዳዮች የተቋቋመው ደርግ ስልጣን ላይ ቁጢጥ ሲል የፖለቲከኞቻችን አይን ተከፈተ። ለካስ ንጉሰነገስት ሳይኮንም ስልጣን ይያዛል አሉ:: ሁሉም በየፊናው ለስልጣን ሽሚያውን ቀጠለ:: ኢህአፓ, መኢሶን ሕወሓት ኦነግ ወዘተ እያለ:: ዘመኑም የመገዳደል የመጨካከን ሆነ::

..................

በዘመነ መሳፍንት የ አገሪቱ ሁኔታ ሲበላሽና እየባሰበት ሲሄድ ህዝቡ ዘንድ አንድ ሃሳብ ስር ይሰዳል። “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን” የሚል ሃሳብ። የህዝቡ መጎሳቆልና የገዢዎቹ ማጋጣነት አንዳንዶቹን ሀቀኞች ሰዎች አስቆጥቶ የህዝቡን ብሶት በመወከል እንዲነሱ ስለገፋፋቸው ተስፋ በትንቢት መልክ ባገሩ አስተጋባ። “ንጉስ ይነሳል። ስሙንም ቴዎድሮስ ይላል። ኢትዮዽያም ካፅናፍ እስካፅናፍ የሰላምና የምህረት አገር ትሆናለች።” እየተባለ ተነዛ። ተዛመተ። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ካሳ ሃይሉ የተባለው ወጣት በ እድሜና በማሰተዋል እየበሰለ ሲሄድ አንድ እውነት በየሄደበት ተደንቅሮ ያፈጥበት የጀመረው። ይኸውም እውነት ባገሪቱ ብጥብጥና ህግ የለሽነት ነግሷል፣ አገሬው የመኳንንቱና የሽፍቶች መጫወቻ ሆኗል፤ ከሽፍቶቹ የማይሻሉት መኳንንት በሹመት የተተከሉበትን ባላገር እህሉንም ሚስቱንም እንዳሰኛቸው ይዘርፉታል። ካሳ ይህ ሁኔታ አንገሸገሸው። ሁሉንም ጥሎ ወደ ቋራው ገባ። ባለትንቢቱ ቴዎድሮስን ለመሆንም ወሰነ።

አሁን በዘመናችን የትኛውም ማስተዋል የሚችል ወጣት አንድ እውነት ፊቱ ተደንቅሯል። ይህ እውነትም ባገሪቱ ጥላቻና መናናቅ ነግሷል፤ ህዝቡን ፖለቲከኞቻችን በውስጣቸው ያለውን ጥላቻና ቂም ማራገፊያ አድርገውታል። ፖለቲከኞቻችን እንደ አንድ አገር ልጆች ሳይሆን እንደ ደመኛ ጠላቶች እየተያዩ በህዝቡ ውስጥ አለመተማመንን መፈራራትን ጥላቻን ዘረኝነትን ዘርተዋል። ታዲያ ይህ እውነት አያንገሸግሽም? ቴዎድሮስንስ መሆን የለብንም?

..............................

የቋራው ካሳ አሸንፎ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ በ ኢትዮዽያ ነገሰ። ......... ዳግማዊ ቴዎድሮስ መጀመሪያ ያወጁት የባሪያ ነፃነትን ነበር። በዚያን ጊዜ ትልቁ የሁዋላ ቅርነታችን መገለጫ የነበረው የባሪያና የጌታ የመደብ ልዩነት አለመቅረቱ ነበር። ካሳ የመጀመሪያው ችግር የሆነውን ለመፍታት እርምጃ ወሰደ። ሰው ሰው ነው፣ ባሪያ ብሎ የሰው ዘር የለም አለ። ታዲያ ይሄን መሳፍንቱና መኳንንቱ ወደዱለት? . . . አልወደዱለትም። ጠላት አፈራ።

አሁን ባገራችን ዋናው የጥላቻና ብጥብጥ ምንጭ ምንድነው? በዚያን ጊዜ ባርነት መፈታት የነበረበት ያገሪቱ ችግር እንደነበር ግልፅ የነበረውን ያክል፤ የ አሁኑ ደግሞ የብሄር ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ነው። የብሄር አጀንዳን ይዘው ጠባብ ብሄርተኝነትን የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞች እንደ አሸን ፈልተዋል። ሆኖም የሁሉም ጥያቄ ጠባብ ብሄርተኝነት ነው ማለት አይቻልም። ስለሆነም አዲሱ ትውልድ (አዲሱ ካሳ) የመጀመሪያ እርምጃው መሆን ያለበት ይህን እስካሁን መፍታት ያቃተንን ችግር አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ መፍታት ነው። ታዲያ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ላይ የተፈጠሩት አይነት ጠላቶች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። መደማመጥ፣ መከባበር፣ የሌላውን አሰተሳሰብ አለማነቋሸሽ ከሁዋላ ይልቅ የፊቱን ማየት ያስፈልጋል።

..........................

--
June 23, 2010 at 9:16 AM Flag Quote & Reply

Tewodros Salsawi
Member
Posts: 24

አፄ ቴዎድሮስ የ እስላምንና የክርስቲያንን ሊቃውንት ደብረታቦር ጃንሜዳ ሰበሰቡ። በ እስላሙ ህብረተሰብ የተከበሩ ሊቅ ሼህ ሁሴን ጂብሪል የተባሉ ነበሩ። በክርስቲያኑ በኩል ደግሞ መምህር አካለወልድ የተባለ ወጣት ሊቅ ነበር። እና ነጉሱ ለሁለቱም ሊቃውንት አንድ ሰንጋ ላኩ። ሰንጋውንም የወሰደላቸውን ባለሟል “የሚያደርጉትን ሁሉ ተመልክተህ መጥተህ እንድትነግረኝ።” ብለው አዘዙት። እንግዲህ ሰንጋውን ማን ይረደው? ሼክ ሁሴን ጂብሪል ተጨነቁ።..... መምህር አካለወልድም “ሼህ ሁሴን ምነው ተጨነቁ? እርስዎ ነዎት ታላቅ ይባርኩት” አላቸው። ቢስሚላሂ ብለው አረዱት። .. ተበለተና ተካፈሉት። ..... መምህር አካለወልድ ድርሻውን ከደቀመዛሙርቱ ጋር በስመ አብ ብለው ባርከው በሉት።........... ጉድ! ተባለ።

.............. ሰንጋውን ያመጣላቸው ባለሟል በታዘዘው መሰረት ወደ ንጉሱ ተመለሰና የሆነውን ሲነግራቸው ....... “መምህር አካለወልድ በስመ አብ ብለው ሲባርኩት ደሙ እንደገና ቷ! ብሎ ፈሰሰ።” አላቸው።

ቴዎድሮስም “እሱን ተወውና በላ? አልበላም?” አሉት

ባለሟል “በሉ”

ቴዎድሮስ “ይማሯል እንዳካልዬ

ይዋጓል እንደገብርዬ” ... ብለው ለመምህር አካለወልድ ያላቸውን አደናቆት ገለፁ። “ሐይማኖትህን በጉያ አገርና እኔ ግን የጋራ ነን”። ብለው ጉባኤውን በተኑት። የሐይማኖት ነፃነት አወጁ ማለት ነው።

ዋናው እዚህ ጋ ማስተዋል ያለብን የተላላኪውን ሚና ነው። ተላላኪው ወሬውን ሙሉ በሙሉ አጣሞ ቢናገር በቴዎድሮስ ባህሪ ሌላ አይነት ታሪክ ሊከሰት ይችል ነበር። ዞሮ ዞሮ ግን ተላላኪው ይችን አጭር ታሪክ እንኳ ውሸት ሳይጨምር ማስተላለፍ እንደከበደው ነው። አዲሱ ትውልድ ከዚህ ታሪክና ከቴዎድሮስ ምን ይማራል?

አሉባልታ አበሾች በረጅም አመታት ምርምር የገነቡት ኒዩክሊየራቸው ሆኖ ይታየኛል። የወሬና ያሉባልታ መሳሪያዎችን የታጠቁ ሰዎች በጣም ሲያጠቁ እኔ እንኳ በዚች አጭር እድሜዬ አይቻለሁ። የሚያሳዝነው እውነተኞች ያንን መሳሪያ ሊታጠቁ አለመቻላቸው ነው። አዲሱ ትውልድ ከ18ኛው ክ/ዘመን ካሳ መማር አለበት። እባካችሁ ...እባካችሁ ለ አሉባልታ ቦታ አንስጠው። ያለበለዚያ ሁላችንንም ያጠፋናል። የ አለም ሃያላን መንግስታት ድሮ አቶሚክ ቦምብ ለመስራት የተሯሯጡትን ያክል አሁን ስለመቀነስ መጨነቅ ጀምረዋል ....... ምክኒያቱም ሁላችንንም ያጠፋናልና። ኢትዮዽያውያንም የኛን አቶሚክ ቦምብ (አሉባልታን) ስለመቀነስ ብቻ ሳይሆን ስለማጥፋት ማሰብ ይኖርብናል ..... ምክኒያቱም ሁላችንንም አንድ ላይ ገደል ሊከተን ይችላልና። ከቶናል እንጂ! ......

የ አገራችን ጋዜጠኞች ሊቀየሩ ይገባቸዋል። ያላረጋገጡትን ወሬ ከማውራት መቆጠብን ይልመዱ፤ የተለያዩ አይነት አመለካከቶችን ማንሸራሸር ገንቢ የሆኑ ሂሶችንና አስተያየቶችን መስጠት፣እውነትን ማውጣት፣ ውሸትን ማጋለጥ መቻል አለባቸው። ከሁሉም በላይ የ ኢትኦዽያ ህዝብ በተለይም አዲሱ ትውልድ የ አሉባልታና የሃሜት ባህሪ ያልተላቀቃቸው አካላት የሚያመጡለትን ወሬና አሉባልታ እንደ ቴዎድሮስ “እሱን ተወው” ማለት መቻል አለበት።

.......................

--
June 23, 2010 at 9:17 AM Flag Quote & Reply

Tewodros Salsawi
Member
Posts: 24

አፄ ቴዎድሮስ መሪነታቸውን እንዳደላደሉ አገር ወደማረጋጋቱ ነበር የገቡት ...... “ልዩ ዘብ ላቋቁም ነውና ሸፍተህ በዱር በገደሉ ከምትንከራተት በሁዋላ ስትያዝ ከምትሰቀል ና ግባ ይሻልሃል ቀለብ እሰፍርልሃለሁ”..... ብለው አዋጅ አስነገሩ። በየዱሩ መሸጎ የነበረውን ሽፍታ ወደህግ መለሱት።

በ አሁኑ ጊዜ የ ኢትዮዽያ ልጆች የዘመኑን ጫካ(የስደትን) ኑሮ ተያየዘውታል። ሁሉም ሸፍቷል ... ወደ ስደት። አዲሱ ትውልድ (አዲሱ ቴዎድሮስ) በስደት ጫካ ወሰጥ ሸፍቶ ያለውን ኢትዮዽያዊ በ አዋጅም በተግባርም ወዳገሩ እንዲመለስ መጋበዝ አለበት። በመካከለኛው ምስራቅ፣ በ አውሮፓና በ አሜሪካ ሸፍተው ያሉ ኢትዮዽያውያንም ለስልጣንና ለግል ጥቅም ሳይሆን ለ አገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ አዲሱን ቴዎድሮስ በመፍጠር መተባበር ይገባቸዋል።

.........................

አፄ ቴዎድሮስ “....ወታደር ሲባል የ አገሪቷና የንጉሰነገስቱ ነው እንጂ የየደጃዝማቹና የራሶቹ የግል ወታደራቸው አይደለም....” ሲሉ አሳወጁ።” ...ራስም ሆነ ደጃዝማች የወታደሮቹ አለቃ ነው እንጂ አሳዳሪ አይደለም። አሳዳሪው የንጉሰነገስቱ መንግስት ነው.....” ብለው እስካሁን ሊተገበር ያልቻለውን የጦር ሰራዊት የህዝብ ታዛዥነት(በጊዜው የንጉሱ) ለመተግበር ሞከሩ።

አዲሱ ትውልድ የሰላም አርአያ መሆን አለበት። ስልጣን ከ60ዎቹ ፖለቲከኞች ሲረከብ በህዝብ ተመርጦና ሰላማዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው መሆን ያለበት። ከዚያም በሁዋላ የ አገሪቱ ሰራዊት ታዛዥነቱ ህዝቡ ለሚመርጠው ሲቪል መንግስት ብቻ ነው መሆን ያለበት።

..........................

አፄ ቴዎድሮስ እንደነገሱ አንድ ፕላውደን የተባለ የ እንግሊዝ መንግስት ልኡክ በ እንግሊዝና በ ኢትዮዽያ ስለሚደረግ የንግድ ልውውጥ ውል ሲያነብላቸው አፍጥጠው ቆመው በጥሞና አዳመጡ .... የውሉ መጨረሻ አንቀጽ እንዲህ ይነበባል “ ..... አንድ የ ኢትዮዽያ ዜጋ በ እንግሊዝ ምድር ወንጀል ቢፈጽም በ እንግሊዝ ፍርድ ቤት ይፈረድበታል፤ አንድ የ እንግሊዝ ዜጋ በ ኢትዮዽያ ምድር ወንጀል ቢፈጽም እሱም በ እንግሊዝ ፍርድ ቤት ይፈረድበታል .......” ይላል። አፄ ቴዎድሮስም “ .... ፖለቲካውን እንደነራስ ዓሊ አልተራቀቅሁበትምና ለነሱ እተወዋለሁ፤ ነገር ግን የመጨረሻውን አንቀፅ አልወደድኩትም። እኩልነታችን የት ላይ ነው? አገሬን ላስከብር እንጂ ለእንግሊዝ ላስገብር አልተነሳሁም .....” ብለው ውሉን አፈረሱ።

ፕላውደንም ለ አገሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዘገባ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል “ .... መመልከት ያለብን ቴዎድሮስ እምቢ ማለታቸውን ሳይሆን እምቢ ያሰኛቸውን ጉዳይ ነው። ምክኒያታቸው ያው የተነሱበት የ አገራቸው ክብርና ኩራት መሆኑን ነው። ይህንንም ተረድተን ውሉ የሚስተካከልበትን መንገድ ማሰብ ይኖርብናል ........”

አሁን በዘመናችን በ አሜሪካና በ አውሮፓ ቁጭ ብለው የ ኢትዮዽያን መንግስት ለመመስረት የሚጥሩ አሉ። የሚገርመው ለመመስረት ማሰባቸው አይደለም፤ ለመመስረትም ይሁንታውን የሚጠብቁት ከ አሜሪካና ከ አውሮፓ መንግስታት መሆኑ ነው። ራሳቸው መዋረዳቸው ሳያንሳቸው የ ኢትዮዽያን ህዝብ የሌሎች አገሮች የበታች(ሆኖ እማያውቀውን) እና ታዛዥ ለማድረግ የሚጥሩ የ አገራችን መንግስትም በ አሜሪካ የሚሾም የሚመስላቸው ወይም እንዲሾም የሚፈልጉ አሉ። .... ያሳዝናል! .... ። በውጪም በውስጥም ያለ ወጣት እንዲህ አይነቱን አመለካከት ከ ኣእምሮው ማስወገድ አለበት። ግዴለም ለሌሎች ከምንሸነፍ ለወገናችን ብንሸነፍ አይሻለንም? ወጣቱ (አዲሱ ቴዎድሮስ) የ አገሩን ህዝብ ጥቅም ከምንም በላይ የሚያስቀድም መሆን አለበት።

.............................

ካሳ (የሁዋላው ቴዎድሮስ) በተለይ በተለይ ዋናውን የ ኢትዮዽያ ህዝብ ችግር አውቆት ነበር። የ ኢትዮዽያ ህዝብን እንደሌሎች ተንኮለኛ መሳፍንት እያሞገሰ አይበዘብዘውም ነበር። የ ኢትዮዽያን ህዝብ የድህነቱ ምክኒያት የሆነውን ስንፍናውን ፊት ለፊት ይነግረው ነበር። መንገርም ብቻ ሳይሆን ከዚህ የስንፍና በሽታ አድነዋለሁ ብሎ ያምን ነበር። እና ጎንደር በጊዜው ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ለተቀረው አገርም አርአያ ነው ብሎ ያስብ ስለነበር “ ...... ጎንደር ... ጎንደር ! ስራን ብቻ ሳይሆን በሰራኸው መኩራትን ጭምር ላስተምርህ እናትህ ሆድ ድረስ እከተልሃለሁ....” ይል ነበር።

እስካሁን የተነሱ መሪዎቻችን፣ ፖለቲከኞቻችን፣ ኢኮኖሚስቶቻችን፣ ምሁሮቻችን በሙሉ ለ ኢትዮዽያ ህዝብ ድህነት የሚያቀርቡት ሰበብ ሁልጊዜ ዋነኛውን ምክኒያት የማያካትት መሆኑ ያስገርመኛል። የ ኢትዮዽያ ህዝብ ለምንድነው ሰላም የሌለው? ለምንድነው በድርቅ የሚጠቃው? ለምንድነው ሁልጊዜ ጦርነት ላይ የሆነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምለሱ “ደሃ ስለሆነ።” ነው። ለምንድነው ድሃ የሆነው ለሚለው ደግሞ ሰነፍ ስለሆነ ነው። ስለዚህ ጥቅላላ የ አገሪቱ ችግሮች በሙሉ መነሻቸው የህዝባችን የስራ ባህል ነው። ለ አሉባልታና ለወሬ የምናውለውን ጉልበት፣ ጊዜ፣ ቦታና ገንዘብ ለስራ ብናውለው የት በደረስን። የ19ኛው ክ/ዘመን ቴዎድሮስ ይህን ችግራችንን ተረድቶልናል። የ አሁኖቹ ቴዎድሮሶችስ ይሄ ይጠፋናል?

አሁን በሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ቴዎድሮስ ይነሳል። ያ ቴዎድሮስ ግን ግለሰብ አይደለም። ቴዎድሮስ አስተሳስብ ነው፤ ቴዎድሮስ እኩልነት ነው፤ ቴዎድሮስ አንድነት ነው፤ ቴዎድሮስ ብልፅግና ነው፤ ከሁሉም ከሁሉም በላይ ቴዎድሮስ ፍቅር ነው!። አሁን ይህን ያነበብክ ያነበብሽ ... አንተ አንቺ .... ቴዎድሮስ ነህ?. ወይስ አይደለህም? .... ቴዎድሮስ ነሽ ወይስ አይደለሽም? ያንተ ... ያንቺ ውሳኔ ነው። ኢትዮዽያ ግን ትጣራለች። በፍቅር፣ በ አንድነት፣ በሰላም አበልፅጉኝ ከሚገባኝ ኖታ አስቀምጡኝ ትላለች ...... መድሃኒቴ አንድ ነው እሱም “ፍቅር” ነው ፍቅርም አንድነት ነው! ትላለች።

ቴዎድሮስ ሳልሳዊ

--
June 23, 2010 at 9:17 AM Flag Quote & Reply

You must login to post.

Share on Facebook

Share on Facebook

The Weather Channel

Quote of the Day

Quote of the Day