|
|
መርስኤ ኪዳን
ግንቦት 15 2002 የተካሄደው ምርጫ ማንም ባልገመተው መልኩ በ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ አሸናፊነት ተጠናቅቋል። ይህ ውጤት ለተለያዩ አካሎች የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። በውጭ አገር ሆነው ሰላማዊ ትግል ዋጋ የለውም ኢህአዴግን በተገኘው መንገድ ሁሉ በማጥቃት መደምሰስ ያሰፈልጋል ለሚሉ ለዚህ አቋማቸው ማረጋገጫ እንደሆነ አድርገው ይወስዱታል። በ አገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ አላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ ለቆዩት ደግሞ በሰላማዊ ትግልና በ አመፅ መካከል አንዱን እንዲመርጡ የሚያስገድድ ሁኔታ ፈጥሯል። የዚህ ፅሁፌ ትኩረት የሚሆነው እነዚህ በሰላማዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች የገጠማቸውን ፈተና ለመዳሰስና በበኩሌ ያዋጣል የሚለውን ለመጠቆም ነው። ወደዋናው ጉዳይ ከማምራቴ በፊት ግን ይህ ያልተጠበቀ ውጤት እንዴት ተከሰተ የሚለውን ለማየት እሞክራለሁ።
ግንቦት 15 በተካሄደው ምርጫ ከ547 ወንበሮች ውስጥ ከሁለት መቀመጫዎች በስተቀር የተቀሩት በሙሉ በኢህአዴግና በአጋሮቹ መያዛቸውን ምርጫ ቦርድ በጊዜያዊ ውጤት መግለጫው አርድቶናል:: አርድቶናል ያልኩበት ምክኒያት ይህ ዜና ለማንም የምስራች ሊሆን ይችላል ብዬ ስለማላስብ ነው:: ገዢው ፓርቲ ራሱ ሊደነግጥና ሊያስብበት የሚገባ ዜና ነው:: ምናልባት የምስራች ከሆነ ሊሆን የሚችለው በውጭ ሆነው የትጥቅ ትግል እናካሂዳለን እያሉ ለሚፎክሩ አካላት ነው:: ከፋም ለማም ይህ ውጤት እንዴት መጣ የሚለውን ለማየት ስሞክር በሶሰት አንኳር ነጥቦች ሊከፈሉ የሚችሉ ምክኒያቶች ናቸው የመጡልኝ::
1. በተቃዋሚዎች መጥፎ ባህሪና መከፋፈል
2. ኢህአዴግ ባለፉት አምስት አመታት ባሳየው መልካም ጅምር
3. በምርጫ ሂደቱ ሚዛናዊ አለመሆንና በኢህአዴግ ጫና
በ1997 ቅንጅትን የመስረቱት አራት ፓርቲዎች የደጋፊያቸውን ድምጽ አራት ቦታ ከመከፋፈል በማዳን በጋራ እጅግ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘት እንደቻሉ ይታወሳል:: ከፍተኛ ድምጽ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ያሳዩት የነበረው ከፍተኛ የመተባበርና የአንድነት መንፈስ የደጋፊያቸውን ስነልቦና በመግዛት እምነት እንዲያሳድር አድርጎ ነበር:: ሆኖም አሁን አንደኛ አራት ቦታ ተከፋፍለው በመምጣታቸው ሁለተኛ ከመከፋፈል ባለፈ እርስ በራስ በጠላትነት መተያየታቸው ጭራሽ ደጋፊያቸውን ተስፋ ከማስቆረጥ ባለፈ ድምጽ እንዲነፍጋቸው አስገድዶታል::
ከፓርቲዎች መብዛት በላይ የተቃዋሚውን ደጋፊ ተስፋ ያስቆረጠው በተቃዋሚዎች መሀል የሚታየው የመረረ ሽኩቻና ጥላቻ ህዝቡ ከሚፈልገው የፍቅር የአንድነትና የመተባበር መንፈስ ጋር አብሮ ሊሄድ አለመቻሉ ነው:: ስለዚህ ከተቃዋሚ ደጋፊው ግማሹ የሚበጀውን እስኪያገኝ መቆጠብ ሲመርጥ ግማሹ ደግሞ ጭራሽ ኢህአዴግን የመረጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ከነችግራቸውም ቢሆን ተቃዋሚዎችን የደገፈው ህዝብ ብዛት ደግሞ ብዙ ቦታ መከፈሉ ለኢህአዴግ አሸናፊነት አንዱ ምክኒያት ሆኗል::
ሌላው ለኢህአዴግ አሸናፊነት አስተዋጽኦ ያደረገው ባለፉት አምስት አመታት በተለይ በኢኮኖሚው የታዩት እመርታዎች ውሱን ቢሆንም የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ወደኢህአዴግ ደጋፊነት የቀየረበት ሁኔታ አለ:: ይህ ተገቢ የሆነ ሂደት ነው:: አንዳንዶች ኢህአዴግን ደጋፊ እንደሌለውና ብቻውን እንደተንሳፈፈ የአገር ጠላት የሚያዩበት ሁኔታ አይገባኝም:: ኢህአዴግ ቀድሞም ሆነ አሁን ብዙ ደጋፊዎች እንዳሉት መደገፍም መብታቸው እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል::
ሶሰተኛውና ከፓርቲዎች እርስ በርስ መከፋፈል ቀጥሎ ለኢህአዴግ አሸናፊነት ምክኒያት የሆነው ኢህአዴግ በምርጫው ሂደት ላይ ያደረገው ጫናና ያልተመጣጠነ ተጽእኖ ነው:: የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች እንዳረጋገጡት ገዢው ፓርቲ የመንግስት ሀብትን ለራሱ መቀስቀሻ ይጠቀም ነበር:: የበለጠ የሚያሳዝነው ሌሎች ፓርቲዎች በክርክር ጊዜ እንኳ ከኢህአዴግ እኩል የመከራከሪያ ሰአት እንዳይመደብላቸው ተደርጎም ኢህአዴግ አልበቃ ብሎት በመንግስት ሜዲያ የቅስቀሳ ፕሮግራሞችን ያደርግ ነበር:: በዚያ ላይ ባለፉት አምስት አመታት በተለያየ ጥቅማጥቅም ያሰባሰባቸው አምስት ሚሊዮን አባላት የተመለመሉበት አኪያሄድ ተገቢ ያልሆነ እና የአንድ ፓርቲ የበላይነት ያሰፈነ ሆኗል:: ከሁሉ የከፋው በምርጫው ቀን እያንዳንዱ የኢህአዴግ አባልና ካድሬ አምስት አምስት ግለሰቦችን ይዞ ሄዶ የድርጅቱ ምልክት የሆነውን ንብን እንዲመርጡ ያደረገበት ሁኔታ የኢህአዴግ አላማ ምን እንደሆነ ግራ እንዲገባን ያደረገ ድርጊት ነው:: የኢህአዴግ ገደብየለሽ ጫና በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ የሚገኙ ሀይሎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ፈጥሯል::
በኢትዮዽያ ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን የሚሉ ብዙ ፓርቲዎች ቢኖሩም በእርግጥ ለሰላማዊ ፖለቲካ ምህዳር መፈጠር ያሚያስፈልገውን መቻቻልንና መከባበርን የሚያሳዩ ጥቂት ናቸው ማለት ይቻላል:: በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ዋና ዋና የፖለቲካ ሀይሎችን ብንመለከት መድረክ የሚባለው የፓርቲዎች ስብስብ ለመቻቻልና ምክኒያታዊ ፖለቲካ መፈጠር ጥረት በማድረግ ፋንታ ጭራሽ ልዩነትን በማስፋትና ገዢውን ፓርቲ ባገኘው መንገድ ማጥቃት ላይ አተኩሯል:: የኢህአዴግም አኪያሄድ በተመሳሳይ መልኩ ያለውን ሀይል ሁሉ ተጠቅሞ አጸፋውን መመለስ ሆኗል:: በዚህም ስትራቴጂ መሰረት አምስት ሚሊዮን ካድሬዎቹን በማሰማራት እያንዳንዱ ካድሬ አምስት አምስት ግለሰቦችን እንዲቆጣጠር በማድረግ ህዝቡ ኢህአዴግን ከመምረጥ ወጪ አማራጭ እንዳይኖረው አድርጎታል:: በዚህ መሀል ለሰላማዊ ትግልና ለመቻቻል ፖለቲካ ቁርጠኛ አቋም የያዙ እንደ ኢዴፓ ያሉ ፓርቲዎችም የቂም በቀሉ በትር ቀማሽ ሆነዋል::
አሁን ከባድ ፈተና ውስጥ የገቡት እነኚሁ ለሰላማዊና የመቻቻል ፖለቲካ ቁርጥ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች እንጂ ሰላማዊ ትግልን አማራጭ ባለመኖሩ ብቻ የሚከተሉት ድሮም ከልባቸው ስላልሰሩበት ብዙም ሊቆጫቸው አይገባም:: አሁን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የገባው ለሰላማዊና ምክኒያታዊ ፖለቲካ ቁርጥ አቋም የያዘው ኢዴፓ ብቻ ሳይሆን ኢዴፓን መሰል ሰላማዊ እንቀሰቃሴ ለማድረግ በቅርብ እንቅስቃሴ የጀመሩ እንደ ኢትዮዽያ ራእይ ፓርቲና ብርሀን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ያሉ ፓርቲዎችም ጭምር ናቸው::
የነኚህ ሰላማዊ ፓርቲዎች ፈተና እንግዲህ ወይ ሰላማዊ ትግሉን በመቀጠል ወይ ከሰላማዊ ትግሉ ውጪ ሌላ አማራጭን በመፈለግ ወይ ደግሞ በመክሰም መካከል አንዱን የመምረጥ ፈተና ነው:: መክሰም የሚለው አማራጭ በተለይ ለአዳዲሶቹ ፓርቲዎች ሊቀል የሚችል ግን በጣም አሳዛኝና ቀስም ሰባሪ ምርጫ ነው:: የነኚህ ፓርቲዎች መክሰም ከስልሳዎቹ ጀምሮ እርስ በራስ ሲበጣበጡና አገሪቱን በጥላቻና በእልህ ሲያናውጡ ለነበሩ ሀይሎች መድረኩን የሚያሰፋና በአገሪቱ አሁን ካለው በከፋ መልኩ የጥላቻ ፖለቲካ እንዲሰፋ የሚያደርግ ነው:: ከሰላማዊ ትግል ውጪ ያሉ አማራጮችን እንዳማራጭ የሚወስዱ ሰዎች በመጀመሪያ አላማቸውን በትክክል ለይተው ማስቀመጥ አለባቸው:: ሰላምን ለማምጣት ከሆነ ሰላም በጦርነት አይመጣም:: አንድነት ከሆነ: ፍቅር በጥላቻ አይመጣም:: ስለሆነም ይህ አማራጭ እንዳማራጭ ራሱ መቅረብ የሌለበት ነው:: እንደከዚህ ቀደሞቹ (የስልሳዎቹ) ፖለቲከኞች አንዱን በጠላት ፈርጆ ለማጥቃት ከሆነ ግን ሊያዋጣ ይችላል::
ምንም እንኳ ከባድ ፈተና ቢገጥመውም በኢትዮዽያ ሰላምን ፍቅርን አንድነትን ለማስፈን ብቸኛውና የሚያዋጣው መንገድ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ነው:: ሆኖም ሰላማዊ ትግል እንደከዚህ ቀደሙ በተበታተነና እርሰበራስ በሚጣረስ መልኩ ከተደረገ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ከ2002ቱ ምርጫ በላይ አስተማሪ ያለ አይመስለኝም:: ስለሆነም እውነተኞቹ ለሰላምና ለመቻቻል የቆሙ ፓርቲዎች አይዲዮሎጂያቸውና መሰረታዊ አስተሳሰባቸው እስከተቀራረበ ድረስ ተቀራርበው መስራትና ግዙፉን ኢህአዴግን በህብረት መግጠም ይኖርባቸዋል:: በተለይ የኢትዮዽያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በአገሪቱ ያሉ ለሰላምና ለመቻቻል ፖለቲካ ዝግጁ የሆኑ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ እንደከዚህ ቀደሙ መሪ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል:: ሰላማዊና ምክኒያታዊ ፖለቲካ ኢህአዴግ መልካም ስለሆነ ወይ መጥፎ ስለሆነ የሚያዝ አቋም ሳይሆን ለሰላም ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ብቸኛው መንገድ ስለሆነ በአስቸጋሪ ጊዜም ቢሆን ሊታገሉለት የሚገባ ነው::
መርስኤ ኪዳን
ግንቦት 2002 ዓ.ም.
mersea.kidan@gmail.com
Categories: View and opinions
The words you entered did not match the given text. Please try again.


Semehal says...
What a (sorry to say) ? analysis is it! Anyone who knows the basics of Ethiopian politics can simply understand that, EPRDF clearly declared that it has no room for those who want to change it in peaceful manner. It spoken and it spoken in a clear manner that everybody who can know politics-101 can understand it. The fact that it was not willing to give room for pseudo oppositions like the so called ?EDP?, which all knows that they cannot be real challenges for the sake of decorating the parliament, tells that there is no willingness to see the real oppositions. Anyway, thanks Mersie for the article though the content is worthless. Next time, please try to make yourself free from a narrow cottage of a ?tiny? party, and see thing as a real analyst. regards

Oops!
Oops, you forgot something.